የጥቁር ገበያ መቆም አለበት ! የኢትዮጵያዉያን ማህበር በአዉሮፓ የገንዘብን መቀየር ይደግፋል !

የብር ኖቶች መቀየር የኢኮኖሚ ሪፎርሙ አካል ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ
——————————————
የብር ኖቶች መቀየር በኢትዮጵያ የተጀመረው የኢኮኖሚ ሪፎርም አካል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላለፉት 23 ዓመታት በስራ ላይ የነበሩት የኢትዮጵያ የብር ኖቶች መቀየራቸውንም ይፋ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ በስራ ላይ ያሉት የብር ኖቶች የተቀየሩ ሲሆን፤ ካሉት የብር ኖቶች በተጨማሪ የ200 ብር ኖት በስራ ላይ እንዲውል ተደርጓል።
በቀለም ደረጃም 200 ብር ሃምራዊ፤ 100 ብር ውሃ ሰማያዊ፤ 50 ብር ቀይ ብርቱካናማ፤ 10 ብር ደግሞ አረንጓዴ ቀለም ይዘዋል።
አሁን ያለው የ5 ብር ኖት በስራ ላይ እንደሚቀጥል የተገለጸ ሲሆን፤ የብር ኖቱ ቀስ በቀስ በሳንቲም እንደሚቀየረም ተጠቁሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንደገለጹት በኢትዮጵያ ተፈጥሮ የነበረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባት ችግር ለመፍታት ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።
በዚህም አሁን ላይ ኢኮኖሚው ከነበረበት የቁልቁለት ጉዞ ተላቆ በማንሰራራት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ የዋጋ ንረትን የመቆጣጠሩ ስራ በሚፈለገው ልክ ማከናወን አልተቻለም ብለዋል።
ከባንክ ውጭ የሚንቀሳቀስ ከፍተኛ ገንዘብ መኖሩ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ እንዳባበሰው ጠቅሰው፤ የብር ኖት መቀየር አይነተኛ መፍትሄ መሆኑን አብራርተዋል።
የገንዘብ ኖቶቹ ለአጠቃቀም ምቹና ረዥም ጊዜያትን እንዲያገለግሉ ተደርገው መሰራታቸውንም ገልጸዋል።
ኖቶቹን በመቀየሩ ስራ ለህትመት ብቻ በአጠቃላይ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገም አብራርተዋል።
ከዚህ ቀደም የወጣውና ከ1ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በቤት ውስጥ አስቀምጦ መገኘትን የሚከለክለው ህግም ይተገበራል ብለዋል።
ከተጠቀሰው ብር በላይ ገንዘብ ሲንቀሳቀስ በቁጥጥር ስር እንደሚውል ጠቁመው፤ በቁጥጥር ስር የዋለው ገንዘብም የጸጥታ ተቋማትን ለማጠናከር የሚውል ይሆናል ብለዋል።
ገንዘቡን በመቀየር ረገድ በህገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ባንኮችና ማናቸውም አካላት ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሳሰቡት።
በተለይ ባንኮች የብር ኖቶቹን በመቀየር ረገድ በህገ-ወጥ ስራ ላይ ተሰማርተው ከተገኙ ጠንካራ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
በዚህ ዙሪያ በየጊዜው ድንገተኛ ፍተሻ እንደሚኖርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የኢዜአ ዘገባ እንዳመለከተው፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ውጭ በጎረቤት ሀገራት ጭምር ከፍተኛ የኢትዮጵያ ብር ተከማችቶ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ይህ ብር ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ ከፍተኛ የቁጥጥር ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አብራርተዋል።
ነባሩን ብር የመቀየሩን ሂደት በሚመለከትም የሶስት ወር ጊዜ መሰጠቱን አውስተዋል።
ነገር ግን 100 ሺህ እና ከዚያ በላይ ብር ያላቸው ሰዎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ መቀየር እንዳለባቸው ነው ያብራሩት።
እስከ 10 ሺህ ብር ድረስ በካሽ የሚቀየር ሲሆን፤ ከአስር ሺህ በላይ ከሆነ ደግሞ “ገንዘቡን ለመቀየር በመጣው ግለሰብ ስም አካውንት ተከፍቶ ይቀመጥለታል” ብለዋል።
የብር ኖቶቹ ላይ ከዚህ በፊት ያልነበሩና የኢትዮጵያን ገጽታ የሚያሳዩ ምልክቶች ተቀምጠዋል።
ለአብነትም በአስር ብር ኖት ላይ ግመል፤ የመቶ ብር ኖት ላይ ደግሞ የሶፍ ኡመር ዋሻና የሀረር ግንብ ይገኛሉ።
አሁን ላይ ያለው የገንዘብ ኖት ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ ስራ ላይ የዋለ ሲሆን በ1997 ዓ.ም የተወሰነ የደህንነት ምልክቶች ማሻሻያ እንደተደረገበት ይታወሳል።

About expeder

Check Also

Letter to Ambassador of the United States in Ethiopia

May 18, 2024 The Honorable Mr. Ervin Massinga Ambassador of the United States to Ethiopia U.S. …

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

− 1 = 7