በአብይ አህመድ የሚመራው የኦሮሙማ መንግስት በዲያስፖራ አባላት ላይ ክስ መሰረተ::

ምርጫውን ለማደናቀፍ በህቡዕ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖችን እኩይ ሴራ ማክሸፉን የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) 6ተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማደናቀፍ በህቡዕ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖችን እኩይ ሴራ ማክሸፉን የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ።

በተለያዩ የውጭ ሀገራት በሚኖሩ አንድ አንድ ጽንፈኛ የዳያስፖራ አባላት የፋይናንስ፣የሃሳብና የሎጀስቲክስ ድጋፎችን በሀገር ውስጥ የአመጽና የግጭት ተልዕኮ ሰጥተው እንዲፈፅሙ በህቡዕ ላደራጇቸው አካላት ስምሪት ሰጥተው ሁከትና ግርግር በመፍጠር 6ተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማደናቀፍ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በእነዚህ በህቡዕ በተደራጁ የአመጽና የግጭት  ቡድኖች ላይ በተደረገው እልህ አስጨራሽ ክትትልም አደረጃጀታቸው፣ አመራሮቹ፣ ለጥፋት ተልዕኮው የተዘጋጁ ሕገወጥ የጦር መሳሪያዎች፣ የተለያዩ ቁሶች፣ የገንዘብ ድጋፍና ዝውውር የተደረገባቸው ማስረጃዎች፤ተልዕኳቸውን የተመለከቱ የተለያዩ መረጃዎችና ማስረጃዎች ተጠናቅረው እርምጃ አየተወሰደ እንደሚገኝም መግለጫው አመልክቷል፡፡

በሀገር ውስጥና በውጭ በህቡዕ የተደራጁት ቡድኖቹ ሀገራዊ ምርጫውን ለማደናቀፍ  ያወጡትን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ከአንድ አንድ የመንግሥት  የፖለቲካና የፀጥታ መዋቅር አባላትና አመራሮች ጋር ምስጢራዊ ግንኙነት በመፍጠር ኢላማ የተደረጉ  ቁልፍ አመራሮችን ለይቶ በመግደል ሀገራዊ ትርምስ ለመፍጠር  የሚያስችል ሴራ  በመጠንሰስ  በድብቅ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን የጋራ ግብረ ሃይሉ በመግለጫው አብራርቷል ፡፡

በዘረጉት የግንኙነት መረብም አመጽና ሁከት በመፍጠር ቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ እንዲደናቀፍ እቅድ ይዘው  ሲንቀሳቀሱ  መቆየታቸውን አመልክቷል።

እንደ መግለጫው ‹‹ስለ አዲስ አበባ ዝም አንልም›› በሚል በውጭና በሀገር ውስጥ በሚገኙ ግለሰቦች የተፈጠረ አደረጃጀት በአዲስ አበባ ለሚገኙ የህቡዕ ቡድኑ አስተባባሪዎች የተለያየ ተልዕኮ ሲሰጥ ነበር፡፡

በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ወጣቶችን በመመልመል እያንዳንዳቸው በሥራቸው እስከ 300 የሚሆኑ አባል ወጣቶችን እንዲያደራጁ በማቀድ የአመጽ ዝግጅት ሲያቀናብሩ ቆይተዋል።

አስተባባሪዎቹ በማህበራዊ ሚዲያ የትስስር ዘዴዎች በየእለቱ  ከውጭ የጥፋት ተልዕኮ ስምሪት በመቀበልና እታች ላሉት አባላት በማስተላለፍ በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ለመመከት የአማራ ህዝብ ታጥቆ መውጣት አለበት የሚሉ ግጭት ቀስቃሽና አነሳሽ መልዕክቶችን ሲያስተላለፉ መቆየታቸውን መግለጫው አመልክቷል።

በተለያዩ የውጭ ሀገራት በሚኖሩ አንድ አንድ  ጽንፈኛ የዳያስፖራ አበላት እንዲሁም በሀገር ውስጥ ባሉ የህቡዕ ቡድኖች አባላትና አመራሮች መሠረታቸውን አዲስ አበባ በማድረግ ቀጣዩን ሀገር አቀፍ ምርጫ በማስተጓጎል የቡድኑ አባላት በአሳቻ ቦታና ጊዜ በመገናኘት ‹‹በአማራ  ተወላጆች ላይ  ያነጣጠረ ግድያ  እና  የህጻናት ደም ላይ የሚደረግ ምርጫ ይቁም››  የሚሉና ሌሎች ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች ያሏቸውን  በራሪ ወረቀቶችን  በመበተን  ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲነሳ  ቅስቀሳ ለማድረግ ሲዘጋጁም ጭምር እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን የጋራ ግብረሃይሉ በላከው መግለጫ ጠቁሟል።

‹‹ስለ አዲስ አበባ ዝም አንልም›› በሚል የሚንቀሳቀሰው ይሄው ቡድን የጥፋት ተልዕኮውን ለማሳካት ያግዘው ዘንድ መረጃዎችን ለመለዋወጥ የማህበራዊ ሚዲያ የትስስር ዘዴዎችን ይጠቀም እንደነበር በተደረገው ክትትል ማወቅ መቻሉንም የጋራ ግብረሃይሉ መግለጫ ይጠቁማል፡፡ በሁለት የማህበራዊ ሚዲያ ቡድኖች በመደራጀት ቅስቀሳ ሲያደረግ ከነበረው ውስጥ አንደኛው ቡድን  1ሺህ 285 አባላት ያሉት ሲሆን፤ ሁለተኛው ቡድን ደግሞ 308 አባላትን ያካተተና ጀርመንና አሜሪካ በሚገኙ የቡድኑ  ጽንፈኛ  አስተባባሪ ዳያስፖራዎች የሚመራ መሆኑንም መግለጫው አብራርቷል።

ሁከትና ግርግር በመፍጠር ቀጣዩን ሀገራዊ ምርጫ በማደናቀፍ በአቋራጭና በሀይል ወደ ስልጠና ለመምጣት ህልም የሰንቀውን ህቡዕ የግንኙነት መረብ የሚንቀሳቀሰውን ሃይል ከሚመሩት መካከል በስነምግባር ችግር ከሰራዊት አባልነት የተሰናበተው ሃምሳ አለቃ ይሁኔ ጀምበሬ አንዱ መሆኑን መግለጫው ጠቁሟል፡፡

ግለሰቡ በሥራ የሚያውቃቸውን አንድ አንድ የሰራዊት አባላት የዕኩይ ሴራው አካል ለማድረግ በመመልመል  መረጃ  የመሰብሰብ እንዲሁም ተልዕኮ እየሰጠ የመንግስት ቁልፍ ከፍተኛ አመራሮችን እንቅስቃሴ የተመለከቱ መረጃዎችን ሲሰበስብ እንደነበር መግለጫው አስረድቷል።

የቀድሞው የሰራዊት አባል የነበረው ኮማንደር ሙሉጌታ ፅጌ ጥላሁን የተባለ ግለሰብም ከሃምሳ አለቃ ይሁኔ ጀምበሬ ጋር በህቡዕ በተደራጀው ቡድን አብሮ የሚንቀሳቀሱ ሲሆን፤ከውጭና ከሀገር ውስጥም በሚደረግላቸው የፋይናንስ፣ የሃሳብና የሎጀስቲክስ ድጋፎች ህገወጥ ተግባሮቹን እንደሚያስተባብሩና እንደሚያቀናጁ በማስረጃ መረጋገጡን መግለጫው አመልክቷል።

ግለሰቦቹ በተደጋጋሚ ከአዲስ አበባ ወደ አማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ  ወጣቶችን ሲመለምሉና ስልጠና ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡

በተጨማሪም በአዲስ አበባና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በትጥቅ የተደገፈ አመፅ  በመፍጠር የተቀናጀ ሁከትና ግጭት ለመቀስቀስ በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ እንደነበርም አትቷል።

ይሁኔ ጀምበሬና እና ግብረአበሩ ኮማንደር ሙሉጌታ ፅጌ  በተለያዩ የውጭ ሀገራት ከሚገኙ በተለይም ደግሞ ጀርመን ከሚኖረው የህቡዕ ቡድኑ አስተባባሪ ከሆነው ተሻለ ከበደ ኢዶ ጋርም መረጃዎችን ይለዋወጡና የጥፋት ተልዕኮም ይቀበሉ ነበር፡፡

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ የዘር  ማጥፋት  ወንጀል እየተፈጸመ ነው በሚል ሽፋን የፖለቲካ ፍላጎታቸውን በሃይል ለማሳካት ‹‹የአማራ ህልውና አስመላሽ ለኢትዮጵያ ንቅናቄ›› የሚል አደረጃጀት ፈጥረው  ሲንቀቀሳቀሱ መቆየታቸውን መግለጫው አመልክቷል።

አሜሪካን ሀገር የሚኖረውና የህቡዕ አደረጃጀቱ አባል በሆነው ፕሮፌሰር አበራ መሸሻ በተባለ ግለሰብም አማካኝነት ህግና ስርዓትን በጣሳ መልኩና በስውር  85 ገፆች ያሉት ህገወጥ አዲስ ረቂቅ ህገመንግስት ማዘጋጃታቸውን የጠቆመው የግብረ ሃይሉ መግለጫ፤ ህገመንግስቱን ለማሳተም አዲስ አበባ በሚኖረው ናደው ዘውዴ በተባለ ግለሰብ የባንክ ሂሳብ ገንዘብ ገቢ ከተደረገ በኋላ የህትመት ስራው ተጠናቆ አንድ ሺህ ኮፒ ሊሰራጭ በዝግጅት ላይ እያለ አጅ ከፍንጅ መያዙን አስታውቋል፡፡

የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል በመግለጫው፤እነዚህ ሃይሎች ለጥፋት እቅዳቸው ተፈጻሚነት  ከአንድ አንድ ተፎካካሪና የገዢው ፓርቲ አባላትና አመራሮች እንዲሁም በስራ ላይ ካሉና ከለቀቁ የጸጥታና ደህንነት ተቋማት አባላት ጋር በመቀናጀት በህቡዕ ከተደራጁ ታጣቂ ቡድኖች ጋር ትስስር ፈጥረው ሀገራዊ ትርምሱን ለመምራት እቅድ አውጥተው ሲሰሩ መቆየታቸውን የግብረሃይሉ መግለጫ አብራርቷል።

በዚህ ህቡዕ የግንኙነት መረብ ውስጥ በጀርመን ሀገር የሚኖሩ 45 ጽንፈኛ ዳያስፖራዎች ተደራጅተው የህገወጥ እንቅስቃሴው አካል ሆነው መገኘታቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡

ግለሰቦቹ በፈጠሩት አደረጃጀት አዲስ አበባ የሚገኘውን “መሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅትን”  በሽፋንነት በመጠቀም ከድርጅቱ ባለቤት ወይዘሮ መሰረት አዛገ ጋር በመመሳጠር በግብረ ሰናይ ድርጅቱ ስም ከውጭ ከቀረጥ ነጻ ከሚያስገቧቸው የትምህርት መርጃ መሳሪያ፣ አልባሳትና ሌሎችም ቁሶች ጋር  የስልክ መጥለፊያዎች፣ የዙም ውይይት መጠቀሚያ መሳሪያዎች ፣ የቴሌ ሰርቨሮችና የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶችን  ወደ ሀገር ውስጥ  በማስገባት ለተደራጁት  የጥፋት ቡድኖቹ እያከፋፈሉ እያሉ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ግብረ ሃይሉ  ባወጣው  መግለጫ  አስታውቋል።

የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይሉ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ በተለያዩ የውጭ ሀገራት በሚኖሩ ጽንፈኛ ዳያስፖራዎች የፋይናንስ፣የሃሳብና የሎጀስቲክስ ድጋፎች እየተደረገላቸው በህቡዕ የተደራጁት የጥፋት ቡድኖች በሀገር ውስጥ በተለይም በአዲስ አበባ በትጥቅ የተደገፈ አመጽ በማካሄድ ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ እንዲደናቀፍ በማድረግ የመንግስትን ስልጣን በአቋራጭ ለመቆጣጠር በማለም የዘረጉት ስውር የግንኙነት መረብ ከጅምሩ በመንግስት  ጥብቅ ክትትል ሲደረግበት የቆየ እንዲሁም ከደህንነትና ከጸጥታ ተቋማት እይታ ያልተሰወረ ስለነበር እኩይ ሴራው ሊጋለጥና ሊከሽፍ ችሏል፡፡

በዚህ ህቡዕ አደረጃጀት ውስጥ በመሳተፍ ሀገርን ወደ ለየለት ቀውስና ትርምስ ለማስገባት ሲንቀሳቀሱና ሲያስተባብሩ የነበሩ ኮማንደር ሙሉጌታ ፅጌ ጥላሁንና ሃምሳ አለቃ ይሁኔ ጀምበሬን ጨምሮ 15 ተጠርጣሪ ግለሰቦች እንዲሁም እኩይ ሴራቸውን ለመፈጸም ያዘጋጇቸውና ሲገለገሉባቸው የነበሩ የተለያዩ ሰነዶች፣በራሪ ወረቀቶች፣ላፕቶፖች፣ዴስክቶፕ ኮምፒዩተሮች፣የጦር መሳሪያዎች፣ የስለት ማሳሪያዎች እና  የተለያዩ የባንክ ደብተሮች  በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በመግለጫው ተመልክቷል፡፡

በተጨማሪም በውጭ በተለያዩ ሀገራት ሆነው ይህንን ህቡዕ አደረጃጀት ሲያስተባበሩ እንዲሁም የፋይናንስ፣የሃሳብና የሎጀስቲክስ ድጋፎችን ሲያደርጉ የነበሩ ፕሮፌሰር አበራ መሸሻ፣ አቶ ተሻለ ከበደ ኢዶ፣ወይዘሮ የሀረርወርቅ ጋሻው፣ አቶ አስፋው ጀቤሳ፣ አቶ መዕረግ፣ አቶ ቢኒያም፣ አቶ ኪሩቤል፣ ወይዘሪት ሊሻን አህመድ፣ ዶ/ር ገነት፣ ወይዘሮ አረጋሽ፣ ኢንጀነር ሊሻን ግዛውና አቶ ሀገሬ አዲስ በወዳጅ ሀገራት ትብበርና  ከኢንተርፖል  ጋር በመቀናጅት  በቁጥጥር ሥር ውለው  በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን  የጋራ ግብረሃይሉ  ባወጣው  መግለጫ አረጋግጧል።

የደህንነትና የፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይሉ ይህንን ህቡዕ አደረጃጀትና የግንኙነት መረብ በመቆጣጠር   የሀገሪቷን አንድነትና ህልውና ከአደጋ ለመጠበቅ በወሰደው እርምጃ ህብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት ላደረገው የተለመደ ትብብር ግብረ ኃይሉ  ላቅ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡

እንዲህ አይነት ሀገርን የማተራመስ ዓላማ ባለው እኩይ ተግባርና ሴራዎች ውስጥ ያሉ አካላትንና ግለሰቦችን በየግዜው እየተከታተሉ ለህዝብ  ይፋ የማድረግና በህግ ተጠያቂ የማድረጉ ተግባርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ግብረ ኃይሉ አሳስቧል፡፡

በኢትዮጵያ አንድነት የማይደራደረውን የአማራን ሕዝብ በመንግሥትና በወንድሞቹ  ላይ  ጥርጣሬ እንዲገባው በማነሳሳት፤ወደ አላአስፈላጊ ቀውስና ግጭት ውስጥ እንዲገባ በማድረግ፤የንፁሀን ዜጎች ዕልቂት እና ከፍተኛ ውድመት እንዲደርስ ለማድረግ በውስጥና በውጭ ሀይሎች በጋር ጥምረት በስውር ሊፈፀም የነበረው ሴራ የከሸፈው በመንግስት አመራር ሰጪነት፤ በደህንነትና በፀጥታ አካላት ጥብቅ ክትትልና እርምጃ፤ በህዝቡ ንቁ ተሳትፎ እንዲሁም  ለሀገራቸው ደህንነትና ጥቅም በማይደራደሩ ሀገር ወዳድ በሆኑ በተለያዩ የውጭ ሀገራት በሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት መሆኑን የጋራ ግብረ ኃይሉ እየገለፀ፤በቀጣይም በሀገራችን ላይ ሊቃጣ የሚችል ተመሳሳይ ሴራ ሲኖር ህብረተሰቡም ሆነ ሀገር ወዳድ ዲያስፖራዎች ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ግብረ ኃይሉ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ ያቀርባል።

የሀገር መከላከያ  ሚኒስቴር፤ የብሔራዊ  መረጃና  ደህንነት  አገልግሎት፤ የፌደራል  ፖሊስ ኮሚሽንና የኢንፎርሜሽን መረብና ደህንነት ኤጀንሲ፡፡

About expeder

Check Also

Letter to Ambassador of the United States in Ethiopia

May 18, 2024 The Honorable Mr. Ervin Massinga Ambassador of the United States to Ethiopia U.S. …

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

38 − = 37