የተሰጠው የ72 ሰዓት በመጠናቀቁ የመጨረሻው ምዕራፍ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡ በተሰጠው የ72 ሰዓት ውስጥም በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ልዩ ኃይል አባላትና ሚሊሻዎች እጃቸውን ለመከላከያ ሠራዊት አባላት መስጠታቸውን፣ ዛሬ ጠዋት ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል፡፡
በርካታ የትግራይ ወጣቶችም የሕወሓትን እኩይ ዓላማ በመረዳት እጃቸውን መሰብሰባቸውን ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ይህ በመጨረሻው ሰዓትም ቢሆን የተወሰደ ኃላፊነት የሚሰማው ውሳኔ ህሊና ካለው ፍጡር የሚጠበቅ ውሳኔ ነው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹የመቀሌና የአካባቢው ሕዝባችን ትጥቁን ፈቶ በቤቱ በመቀመጥና ከወታደራዊ ዒላማዎች በመራቅ አስፈላጊውን ሁሉ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን፤›› ብለው፣ በጥቂት የሕወሓት አመራሮች ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ሕዝቡ አሳልፎ እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡