የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አዲስ ኮሚሽነር ተሾመለት

የኢንቨስትመንት ኮሚሽንን ለአንድ አመት ከመንፈቅ ሲመሩ በነበሩት አቶ አበበ አበባየሁ ምትክ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንን ሲመሩ የነበሩት ሌሊሴ ኔሜ ተተኩ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሹመቱ ከነገ ሰኔ 16፤ 2012 ጀምሮ እንዲጸና መወሰናቸውን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ታማኝ ምንጮች ተናግረዋል።

አዲሷ ተሿሚ ሌሊሴ ከሚያዝያ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው ሲሰሩ ነበር፡፡ ከዚያ ቀደም ብሎ በኦሮሚያ ክልል የኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም የኦሮሚያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው ሰርተዋል።

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ምህንድስና ያገኙት ሌሊሴ በተማሩበት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም መምህር ሆነው አገልግለዋል። በኦሮሚያ ክልል መንግስት ሹመት ከማግኘታቸው በፊት በጅማ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ውስጥ የሲቪል እና ኢንቫይሮመንት ምህድንስና የትምህርት ከፍል ረዳት መምህር ሆነው አስተምረዋል። ሌሊሴ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በቢዝነስ አሰተዳደር ያገኙት በአሜሪካ ከሚገኘው አሽላንድ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ትምህርት ከሚሰጠው የሊድስታር የአስተዳደር እና አመራር ኮሌጅ ነው።


ተሰናባቹ ኮሚሽነር አቶ አበበ ወደ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከመምጣታቸው ቀደም ብሎ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የህግ አማካሪ ሆነው ሰርተዋል። ከዚያ ቀደም ብሎ በነበሩት ዓመታት በስተኋላ በኮሚሽነርነት በመሩት የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ውስጥ ሲያገለግሉ ቆይተዋል። የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ሆነው በሰሩበት ወቅት የፖሊሲ ጥናት፣ የኢንቨስትመንት ማስተዋወቅ፣ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለውጥ እንዲሁም የኮሚሽኑ የስራ መዋቅር ለውጥ ዘርፎችን መርተዋል።

አቶ አበበ ኮሚሽኑን ከመቀላቀላቸው በፊት በአለም ባንክ በአለማቀፉ የፋይናንስ ትብብር (አይ. ኤፍ. ሲ) በተለይም በኢትዮጵያ በመንግስት እና በግሉ ዘርፍ መካከል አጋርነትን ለማጠናከር ባለሙ መዋቅራዊ ስራዎች ላይ ተሳትፈዋል። በአጠቃላይ ለ15 ዓመታት በግሉ ዘርፍ ልማት ላይ አተኩረውም ሰርተዋል።

አበበ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ በመሆን አጠናቅቀዋል። ቀጥሎም የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከደቡብ አፍሪካው ዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርሲቲ በአለም አቀፍ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ህግ አግኝተዋል። በተጨማሪም ከብሪታንያው ደንዲ ዩኒቨርሲቲ በኢነርጂ ህግ እና ፖሊሲ የማስተርስ ዲግሪያቸውን አጥንተዋል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ሹመቱን በተመለከተ አቶ አበበንም ሆነ ሌሊሴን ብታነጋግርም ሁለቱም በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል። ሹመቱን ያረጋገጡ ታማኝ ምንጮች እንደገለጹት ግን አቶ አበበ በመንግስት የስራ ኃላፊነት ከዚህ በኋላ አይቀጥሉም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

About expeder

Check Also

Letter to Ambassador of the United States in Ethiopia

May 18, 2024 The Honorable Mr. Ervin Massinga Ambassador of the United States to Ethiopia U.S. …

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

3 + 6 =