ግልፅ ደብዳቤ ለዶ/ር አቢይ አህመድ

ነሐሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም.
ግልጽ ደብዳቤ ለክቡር ዶክተር አብይ አሕመድ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር
አዲስ አበባ
ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ ሰላምታችንን አስቀድመን እናቀርባለን።
በመጀምርያ ስለ እኛ ማንነት በጥቂቱ እንግለጽልዎ፣ እርስዎም የሚወዷት ውድ ኢትዮጵያን አብዝተን የምንወድ በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገራችን ወጥተን በየአህጉራቱ የተበተንን፣ በተለያዩ የሙያ መስኮች የሠለጠንንና በመሰልጠንም ላይ የሚገኙ ወጣቶች የሚገኙብን፤ በእካል ከኢትዮጵያችን በብዙ ሺህ ማይሎች ብንርቅም ዘወትር በጸሎታችንና በሀሳባችን የማንለያት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ነን። በሣምንት አንድ ጊዜ ዘመኑ ባስገኘልን ቴክኖሎጂ የፓልቶክ የመወያያ ዘዴ በ‘’ቅንጂት ስዊዘርላንድ የመወያያ መድረክ’’ እየተገናኘን እንመካከራለን፤ ለሀገራችን በየጊዜው ከምናደርጋቸው የገንዘብና ቁሳቁሳዊ አስተዋጽዖ በተጨማሪ ለውጡን እንዴት አድርገን ማገዝ እንደምንችል ሀሳብ እያዋጣን እንመካከራለን፤ እንዲያው ለርስዎ ይኽን አደረግን አይባልም እንጂ በየምንኖርባቸው አገሮች ተደራጅተን በንዋይም ሆነ በሙያ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙ አድርገናል በማድረግ ለይም እንገኛለን። ለህዳሴ ግድብ ቦንድ የገዛን፤ ለ EDTF የበኩላችንን ያደረኝ ብዙዎች ነን።
ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር አብይ፤ የሀገራችን ሰላም፣የሕዝባችን ደህንነት ብሎም የኢትዮጵያ አንድነት ያሳስበናል። የመንግሥትዎ ቸልተኝነት ደግሞ በአያሌው አስደንግጦናል። የሕግ የበላይነት የሚባል ነገር በፍጹም የማይከበርበት ሀገር ስትሆን ማየቱና መስማቱ አሳምሞናል። በቅርቡ በዘፋኝ ሀጫሉ ሁንዴሳ ላይ የተፈጸመው አሳዛኝ ግድያን ምክንያት አድርጎ በኦሮምያ ክልል የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል በዚህ ምእተ ዓለም ውስጥ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ሆኖ እንደማያውቅ ተንቀሳቃሽ ምስሎቹን ያዩ ሁሉ የሚስማሙበት ነው። ሰው ሰውን አረዶ ቤት ንብረቱን አቃጥሎ ከሞት የተረፈውን የቤተሰብ አካል አንተ መጤ ነህ እዚህ ልትኖር አይገባም እያለ በገዛ ሀገሩ መግቢያ መውጫ ሲያሳጣው፣ መስማትና ማየት ለእኛ በመልክ፣ በቀለምም ሆነ በታሪክ የማይመስሉን ሀገራት በጥገኝነት መጥተንባቸው በሰላም ለምንኖር ሰዎች አስደግጦናል በእጅጉ አሳፍሮናልም። ጥንታዊት ኢትዮጵያ የሦስቱም ታላላቅ እምነቶች ሀገር፤ የመቻቻል ተምሳሌት የነበረች ኢትዮጵያ ዛሬ ምነው የአውሬ መፈንጫ ሆነች? ብሎ መጠየቁ የዋህነት ቢመስልም ያ ሁሉ ሕዝበ ክርስቲያን ሲጨፈጨፍና ንብረት ሲወድም የክልሉ ሕግ አስከባሪዎች የት ሄደው ነው? የፌደራሉስ?፤ ገዳዮች የስም ዝርዝር ይዘው እየመረጡ በአማርኛ ተናጋሪውና ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኙ ላይ ጭፍጨፋ ሲያካሂዱ የመንግሥትዎና የክልል መንግሥት ተብዬው ዝምታ ጭካኔ ብቻ ሳይሆን ከገዳዮች ጋር መተባበርን ያመላክታል የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። ይጣራ።
ከዚህ ሀዘን ሳንወጣ፣ ጠቅላይ ሚንስትራችን ከአሁን አሁን የተጎዳውን አካባቢና ወገን ሄደው ያጽናናሉ፤ የሀገሪቱ ሰንደቅ አላማም ለተወሰኑ ቀናት ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ፣ ለተፈናቀሉና ቤት ንብረታቸውን ላጡ ቢያንስ ጊዜያዊ መጠለያ እንዲዘጋጅላቸው ያደርጋሉ፣ ለዚህ የዘር ማጥፋት/ማጽዳት ጭፍጨፋ ዋናው ተጠያቂ በአቶ ሽመልስ አብዲሳ የሚመራው የኦሮምያ ክልል መንግሥት ስለሆነ ይቅርታ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ንብረታቸው የወደመባቸውን ክሶ ወንጀለኞችን ለፍርድ ያቀርባል ብለን ስንጠባበቅ፤ የአቶ ሽመልስ የናዚዎችን የ1933 Final Solution”, መሰል ንግግር አፈትልኮ ወጥቶ ሰማነው።
ለካ ከ8 ወራት በፊት የታቀደውና በሚስጥር የተነገረው እየተተገበረ ነው?
እውነት ነው አቶ ሽመልስ ክፉኛ ግራ አጋብቶናል። እውነት የፓርቲዎ መመርያ አቶ ሽመልስ እንዳለው ነው? ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ይኽ ሁሉ ከምናውቀው የክቡርነትዎ ስብዕና ጋር ከቶውንም አይሄድም፤ ትዕግሥትን እንደ ፍርሃት ደግነትን እንደ ሞኝነት የሚቆጥሩ ብልጣ ብልጦች ‘’አይብ ሲያድር አጥንት ይሆናል’’ ሆነው ይሆን?። ትግላቸው ሁሉ ለእኩልነት ሳይሆን ለበላይነት እንደሆነ እያየንና እየሰማን ዝምታው እስከ መቼ? እርስዎም በተደጋጋሚ እንደሚሉት ሁሉም ሰው፣ባለሥልጣናትም ጭምር ከሕግ በታች እንጂ በላይ አይደሉም እና ስለሕግ የበለይነት ብለው እባክዎ ሕግና ሰብአዊ መብትን አስከብሩልን!
ስለዚህ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር፣
ሀ. ወንጀለኞችና እጃቸው ያለበት ባለሥልጣናት፤ በቸልተኝነት የእልቂቱ ተባባሪ የሆኑ በአስቸኳይ ለፍርድ ይቅረቡ፣
ለ. ቤተሰቦቻቸው ለተገደሉባቸው፣ለተጎዱባቸውና ንብረታቸው ለወደመባቸው የክልሉ መንግሥት ካሣ እንዲከፈል፤
ሐ. ለተፈናቃዮች ፣ አስፈላጊው ቁሳቁስና መጠለያ ከተሟላ ጥበቃ/ዋስትና ጋር እንዲዘጋጅላቸው
መ. አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ፤ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ የትንኮሳ ንግግር ላደረጉት ተጠያቂ እንዲሆኑና ለፍርድ እንዲቀርቡ፣
ረ. ብሔራዊ የሀዘን ቀን ታውጆ ሰንደቅ ዓላማችን ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ፤
በመጨረሻም የጥላቻ እና ለፍጅት ቅስቀሳ የሚያደርጉ በሙሉ እኩይ ተግባራቸው ስር ሳይሰድ ለፍርድ እንዲቀርቡ በትህትና እንጠይቃለን።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፤ ይጠብቅ።
አንድነት፣ የቅንጅት ስዊዘርላንድ የውይይት መድረክ አስተዳደርና ታዳሚዎች ዙሪክ/ ስዊዘርላንድ

About expeder

Check Also

Letter to Ambassador of the United States in Ethiopia

May 18, 2024 The Honorable Mr. Ervin Massinga Ambassador of the United States to Ethiopia U.S. …

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

27 + = 29