Ethiopian Stock Market – የኢትዮጵያ የስቶክ ገበያ

ኢትዮጵያ የስቶክ ገበያን ለመጀመር የሚያስችላትን ጥናቶች እና ውይይቶች እያካሄደች ትገኛለች። ሀገሪቷ በአፍሪካ በኢኮኖሚ እያደጉ ካሉት ሀገራት መካከል አንዷ ብትሆንም እና አንድ አስረኛ የሚሆነው የአፍሪካ የሸማቾች ሀብት ባለቤት ብትሆንም እስካሁን ኢኮኖሚዋ ለስቶክ ማርኬት ክፍት አልበረም።

በኢትዮጵያ የስቶክ ማርኬትን የማቋቋም ጉዳይ በምሁራን፣ በመንግስት አካላት እና በኢኮኖሚዉ ተዋናዮች ዘንድ ከፍተኛ የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል። በጉዳዩ ላይ የተለያዩ የዘርፉ ባለሙያዎች ምርምር ሲያደርጉ እና ጥናቶችን ሲሰሩ ቆይተዋል። በሐምሌ 2021ዓ.ም. ደግሞ በብሄራዊ ባንክ መሪነት የስቶክ ማርኬትን አጀማመር በተመለከተ የውይይት ሴሚናር በሸራተን አዲስ ተካሂዷል። የብሄራዊ ባንክ ስቶክ ማርኬት በኢትዮጵያ ሊቋቋም ጫፍ መድረሱን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሱፐርቪዥን ዳይሬክተር አቶ ፍሬዘር አያሌው ለአዲስ ዘይቤ እንደገለጹት፣ ይህ በ 2021 መጨረሻ ለማሳካት የታቀደው የስቶክ ማርኬት ገበያን በይፋ የመጀመር ስራ ከፋይናንስ ግብይቶች ጋር በተያያዘ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አተገባበርን ያሻሽላል ተብሎ ይጠበቃል። ኢ-ኮሜርስን እና ዲጂታል ፋይናንስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ የካፒታል ገበያን ለመጀመር የሚያስችል ስርዓት መሆኑንም ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ “በዚህ ረገድ እንደ ተግዳሮቶች ሊቆጠሩ የሚችሉ የሕግ እና የፋይናንስ መሠረተ ልማት ያሉ መሰናክሎች ቢያጋጥሙም እነዛን ተግዳሮቶች ለማለፍ የሚቻልባቸው የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያን የሚያካትት የንግድ ፋይናንስ እቅዶች ተዘርግተዋል” ብለዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ የአክሲዮን ገበያ የሌላት ነገር ግን ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ትልቅ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) ካላቸው ሀገራት አንዷ መሆኗ እርግጥ በመሆኑ ይህ የአክሲዮን ገበያን የመጀመር ዕቅድ ምንም እንኳን ፈታኝ ቢሆንም በአጠቃላይ ለአህጉሪቱ ኢኮኖሚ በተለይም ከዓለም አቀፉ የንግድ ስርዓት ጋር የሚኖረውን መስተጋብር ለማሳደግ ላቅ ያለ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

የአክሲዮን ገበያው ያመጣል ተብሎ ከሚታሰበው ኢኮኖሚያዊ እሴት በተጨማሪ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይህ ገበያ መጀመሩ የካፒታልን እድገት በኢኮኖሚ ውስጥ የሀብት ክፍፍልን ያመቻቻል ብለው የሚደግፉ እንዳሉ ሁሉ በካፒታል ገበያዎች ውስጥ የመሳተፍ አቅም ያላቸው ጥቂት ኩባንያዎች ባሉባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ውስጥ የስቶክ ገበያዎች መጀመር በጎ ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ አይኖራቸውም ሲሉ የሚቃወሙ ባለሙያዎችም አሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር መታሰቢያ ሀይሉ የአክሲዮን ገበያው ለተለያዩ ግለሰቦች በር ይከፍታል ፣ ኩባንያዎችም ካፒታል እንዲያከማቹ እና መንግሥት ከግብር በፊት ከሚያገኘው የበለጠ ገቢ እንዲያገኙ ያደርጋል ብለዉ ያምናሉ።

“የተወሰነ የካፒታል መጠን በማበርከት ሰዎች የኩባንያ ባለቤት እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። በዚህ መንገድ ግለሰቦች ገንዘባቸዉን የበለጠ ኢንቨስት ለማድረግ ወይም አክሲዮኖቻቸውን ለመሸጥ ዕድላቸውን ያገኛሉ” ይላሉ።

አክለውም የአክሲዮን ገበያው ሁለተኛ ገበያ ተብሎ የሚታወቀውን የግብይት አሰራር ለመፍጠር የሚያስችል ዘዴ ነው ይላሉ። “በአሁኑ ወቅት ባለአክሲዮኖች አክሲዮናቸውን የሚሸጡበት ዘዴ የለም። ዋናው ገበያ ኩባንያዎች አክሲዮኖቻቸውን የሚሸጡበት ነው ስለሆነም ባለአክሲዮኖች አክሲዮኖቻቸውን የመሸጥ መብት የላቸውም ነበር። ስለዚህ የአክሲዮን ገበያ ወይም የሁለተኛ ገበያ መኖር ይህንን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ይለውጠዋል” ሲሉ ያብራራሉ።

በተጨማሪም ፣ ሁለተኛ ገበያዎች ሌሎች አዳዲስ ነጋዴዎች በአዲሱ የንግድ ሥራ ላይ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ እና የኩባንያቸውን ካፒታል የበለጠ እንዲያሳድጉ ዕድል ይሰጣቸዋል ሲሉ ኢኮኖሚስቱ ያነሳሉ።

“እስካሁን ድረስ እንዲህ ዓይነት ገበያ በኢትዮጵያ ውስጥ የለም። ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ሀገር ሆና የአክሲዮን ገበያ የሌላት ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ ልትሆን ትችላለች።” ሲሉም ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

እንደ ዶ/ር መታሰቢያ ገለፃ የአክሲዮን ገበያ መጀመሩ የመንግሥት ገቢን በግብር መልክ በከፍተኛ ሁኔታ ከፍ እንዲል የማድረግ ሚናም አለው። በመሆኑም በዚህ ሂደት የኩባንያዎች ሀብት ሲጨምር የመንግሥት ገቢ እንዲሁ ይጨምራል። “ነገር ግን ማንም ሰው ዝም ብሎ መጥቶ በአክሲዮን ገበያው ውስጥ መሳተፍ ስለማይችል ፣ መጀመሪያ ይህንን ለማድረግ የሚያስፈልጉ መስፈርቶች መዘጋጀት አለባቸው” ሲሉም አስተያየታቸውን ተናግረዋል።

በባንክ እና በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የካበተ ልምድ ያላቸው የንግድ ሥራ ባለሙያ የሆኑት ዘማች ንዳ ፣ በኢትዮጵያ የአክሲዮን ገበያ መመሥረትን ለማጥናት የከፍተኛ ባለሙያዎች ቡድን አቋቁመው ሥራ ላይ እንደሚገኙ ነግረውናል።

በአክሲዮን ገበያ ላይ የሚስተዋለውን የመተማመን ማነስ ፣ የአክሲዮን ገበያን አሠራር የመረዳት እጥረትና ያደጉ ሀገራት የሚኖራቸውን በጎም ሆነ የተቃውሞ ሙግት ከግምት ውስጥ በማስገባት መስራት ያስፈልጋል በማለት “እንዲህ ዓይነቱ የርዕዮተ-ዓለም አቋም ቀደም ሲል በተለያዩ ሀገራት የአክሲዮን ገበያ እድገት እንቅፋት ሆኖ ስለታየ ጥናቶቹ ጥልቅ መሆን ይገባቸዋል” ብለዋል።

“ሆኖም የአክሲዮን ገበያው ካፒታሊስቶች ከፊት ወንበር ላይ የሚገቡበት ቦታ ነው። በዚህ ሂደት የፋይናንስ ፍሰቱ የሚወሰነው በመንግሥት ሳይሆን በሕዝብ ፈቃድ ነው፤›› በማለት አክለዋል።

እንደ ዘማች ገለፃ የአክሲዮን ገበያው መጀመሩ የሀብት አጠቃቀምን እና የገንዘብ አያያዝን ያሻሽላል በተጨማሪም ባለሀብቶች ገንዘባቸውን በሚፈልጉበት ቦታ ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ይረዳል። እንዲሁም የውጭ ካፒታልን ወደ አገሪቱ ይስባል። ነገር ግን አንዳንድ የአክሲዮን ገበያ መኖርን አሉታዊ ጎኖች ሊያሳድጉ የሚችሉ ሙግቶች ሊሰፉ ይችላሉ እና ጥቅሞቹ ከጉዳት የበለጡ በመሆናቸው አሉታዊ ሙግቶችን ለማሸነፍ መሰራት አለበት ሲሉ ያሳስባሉ።

ከዚህ ጋር በተያያዘ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች ውስጥ የአክሲዮን ገበያ መመሥረት የለበትም ከሚሉት ወገን መካከልም አዲስ ዘይቤ አነጋግራለች።

ኢኮኖሚስት እና ፖለቲከኛ አቶ ክቡር ገናን እንዳነጋገርናቸው በካፒታል ገበያዎች ለመሰማራት መስፈርቱን የሚያሟሉ ኩባንያዎች ቁጥር ውስን በመሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ የአክሲዮን ገበያን ለማቋቋም ትክክለኛው ጊዜ አይደለም ብለዉ ያስባሉ።

መስፈርቶቹ ደንቦችን እና ህጎችን ማክበር ፣ ግብር መክፈል እና ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የሚያሟሉ የ’ቡክ ኪፒንግ’ ስርዓት መኖርን ያካትታሉ። “ለምሳሌ አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ግብርን ለመሸሽ ሲሉ ትርፋቸውን ለመግለጽ ፈቃደኞች አይደሉም። ስለሆነም በብቃት ሊሳተፉበት የሚችሉት ጥቂት ኩባንያዎች በመሆናቸው የካፒታል/ የአክሲዮን ገበያዎች በሀገሪቱ ውስጥ ለሚኖራቸው ለኢኮኖሚ ልማት እና ለሀብት ክፍፍል በጣም ውስን ሚና ይኖራቸዋል ”ሲሉ ክቡር ተናግረዋል።

እንደ አቶ ክቡር ገለፃ ፣ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች የአክሲዮን ገበያዎችን ቢጀምሩም በደንብ የተደራጀ የፋይናንስ ሥርዓት ስለሌላቸው ለኢኮኖሚው ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ እያደረጉ አይደለም። አክለውም “ሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ አነስተኛ የካፒታል ገበያዎች ናቸው። በመጀመሪያ ደረጃ የውጭ ኩባንያዎችን ወደ ካፒታል ገበያው ለመሳብ እና የአክሲዮን ገበያን ለማሳደግ በኢትዮጵያ ውስጥ በርከት ያሉ ትላልቅ ኩባንያዎች ግዴታ ሊኖሩ ይገባል ” ብለዋል።

በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት አሉ የሚባሉት ኩባንያዎች አክሲዮኖች በጥቂቶች እጅ ውስጥ እንደሆኑ እና እነዚህ ጥቂቶች አስቀድመው ብዙ የአክሲዮን ባለቤት በመሆናቸው በአሁኑ ወቅት የሚነግዱበት እና የሚገበያዩበት መንገድ ስለሌለ የካፒታል ገበያዎች እንዲቋቋሙ የሚጠይቁት ቡድኖችም ራሳቸው ናቸው ሲሉ “ይሄ የጥቂቶችን ፍላጎት ሲያሟላ የብዙዎቹን የተዳከመ ኢኮኖሚ ደግሞ ያባብሳል” ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ፍሬዘር አያሌው ኢትዮጵያ የዓለም ኢኮኖሚ አካል በመሆኗ ይሄ የአክሲዮን ገበያ ያስፈልጋታል ሲሉ የአቶ ክቡርን ሃሳብ ይቃወማሉ።

“እኛ የዓለም ኢኮኖሚ አካል እንደመሆናችን፡ ያን ያህል የተለየ አሰራር መከተሉ ልክ አይደለም። የዓለም ንግድ ድርጅትን እየተቀላቀልን በመሆኑ ወደ ዓለም አቀፍ የካፒታል ገበያ ክለብ መቀላቀሉ ይጠቅማል። ከእኛ የበለጠ ጂዲፒ ያላቸው ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ብቻ ናቸው። ስለዚህ ያለንን ሀብት ለመጠቀም ጊዜው ነው” ሲሉ ይህን የአክሲዮን ገበያ ለመጀመር ተመዝግበው ለመሳተፍ ዝግጁ የሆኑ በቂ ኩባንያዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል።

እንደ ፍሬዘር ገለፃ ፣ የተሳካ የካፒታል ገበያ ለማካሄድ የሚያስፈልጉ በርካታ አዳዲስ ተቋማት ያሉ ሲሆን የአክሲዮን ልውውጡ በግሉ ዘርፍ ሊካተት ቢችልም ህግና ደንቡ ግን በመንግስት ይደነገጋል። “የአክሲዮን ደላሎች ድርጅቶች እና የኢንቨስትመንት ባንኮች ይኖሩናል። በዛም ለአክሲዮን ነጋዴዎች በምንሰጠው ሥልጠና የሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ድርጅቶች አቅማቸውን መገንባት አለባቸው”ብለዋል።

source: Nigist Berta – አዲስ ዘይቤ

About expeder

Check Also

Letter to Ambassador of the United States in Ethiopia

May 18, 2024 The Honorable Mr. Ervin Massinga Ambassador of the United States to Ethiopia U.S. …

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

65 − 56 =